መግቢያ፣
በቅርቡ ፒቱፒ (P2P) በሚባለው የትውልደ-ኢትዮጵያውያን ምሁራን ውይይት መድረክ ላይ “አንድ ጥያቄ አለኝ፣ መልስ
እሻለሁ” በማለት የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖሊቲካ ሁኔታ አስመልክተው አቶ በቀለ ገብርኤል የተባሉ የመድረኩ ደንበኛ አጭር
ጥያቄ አቅርበው መልስ በማጣታቸው በቅሬታ መልክ ላነሱት ጥያቄ ራሳቸው መልስ ሲያዘጋጁ ሁላችንም አስተውለነዋል።
ከዚህ ቁጥራቸው እጅግ በጣም ብዙ የሆኑ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሑራንን ካቀፈ የውይይት መድረክ
ውስጥ እንዴት አንድ እንኳ መልስ ሊሠጥ የሚችል ግለ ሰብ ይጠፋል በማለት አብዛኞቻችን ምናልባት ከራሳችን ጋር ሙግት
ገጥመን ይሆናል። እንደ ገመትኩት ከሆነ፣ ጥያቄው መላሽ ያጣው፣ በክብደቱ ምክንያት ሳይሆን፣ ምናልባትም ጥያቄውን
ለመመለስ በራሳችን ላይ እምነት ከማጣት ይመስለኛል። በግሌ ለብዙ ዓመታት ተመሳሳይ ጥያቄዎችን አንስቼ ከትውልደ
ኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ ጋር ረዘም ላለ ጊዜ የተወያየሁበትና እስከ ዛሬም ድረስ አጥጋቢ መልስ ያላገኘሁበት፣ ሲያዩት ቀላል
የሚመስል ሲሸከሙት ግን ከባድ የሆነ ጥያቄ ሆኖ ስላገኘሁት፣ ከፒቱፒ ምርጥ ምሁራን መሃል፣ ለአቶ በቀለ ጥያቄ ደፍሮ
መልስ የሚሠጥ አንድም ሰው አለመገኘቱ አልገረመኝም። ዛሬ የደረስኩበት ድምዳሜ፣ ለዚህ ጥያቄ ተገቢውን መልስ ሊሠጡ
የሚችሉት እኛ ባሕር ማዶ ያለነው ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ አገር ዜጎች ሳንሆን እዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ፣
በያመቱ ግብር በመክፈል የዜግነት ግዴታቸውን የሚወጡና ማኅበራዊና ፖሊቲካዊ ቀውሱ ያስከተለውን ገፈት በየቀኑ
የሚቀምሱ የኢትዮጵያ ዜጎች ብቻ ናቸው የሚል ነው። በኔ ግምት አቶ በቀለ፣ አግባብ ያለውን ጥያቄ አግባብ ባልሆነ ቦታ
የማያገባቸውን ግለ ሰቦች በመጠየቃቸው አግባብ ያለው መልስ ሊያገኙ አልቻሉም ባይ ነኝ። ትንሽ ላብራራ!
