የአገራችንን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ የሚጠበቅብንን ድርሻ እንወጣለን ሲሉ በስዊዘርላንድ የሚኖሩ የዳያሰፖራ አባላት ገለጹ

(ጳጉሜ 3 ቀን 2014) የአገራችንን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ከመንግስት ጎን በመቆም የሚጠበቅብንን ድርሻ እንወጣለን ሲሉ በስዊዘርላንድ፣ በኦስትሪያ፣ በሩማኒያ እና ሀንጋሪ የሚኖሩ የዳያሰፖራ አባላት በሚሲዮኑ በተዘጋጀው የዙም ውይይት ላይ ገልጸዋል::

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር አምባሳደር ዘነበ ከበደ የአገራችንን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ እና ገለጻ አድርገዋል:: ክቡር አምባሳደር ዘነበ በተለይም የህ.ወ.ኃ.ት ሽብር ቡድን የኢትዮጵያን ሰላም ለመንሳት ከውስጥና ከውጭ ተባባሪ ሃይሎች ጋር በመቀናጀት በቅርቡ የጀመረውን የ3ኛ ዙር ወረራ ተከትሎ በመንግስት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን እንዲሁም በአገራችን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን በውጭ ከሚኖረው ዳያስፖራ የሚጠበቁ ጉዳዮችን በተመለከተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል::

ክቡር አምባሳደር ዘነበ በገለጻቸው ማጠቃለያም ሚሲዮኑ በሚከታተላቸው አገራት የሚኖሩ ሁሉም ኢትዮጵያዊን፣ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች አገራችን የምትገኝበትን ነባራዊ ሁኔታ በውል በመረዳት እስከዛሬ ድረስ እያደረጉ ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል::

ገለጸውን ተከትሎ ከተሳታፊዎች የተለያዩ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የተነሱ ሲሆን፤ ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽ እና ተጨማሪ ማብራሪያ ተሰጠቷል::

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የኢትዮጵያን እውነተኛ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማስተዋወቅ በኩል ከዚህ በፊት የጀመሩትን እንቅስቃሴ አጠናከረው በማስቀጠል የተለያዩ መድረኮችን በመጠቀም፤ በማህበራዊ ሚዲያ እና በሌሎች የሚዲያ ተቋማት ላይ በቀጥታ በመሳተፍ፤ እንዲሁም አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ሁሉ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት ከምንጊዜውም በተሻለ እንደሚንቀሳቀሱ አረጋግጠዋል::

በተጨማሪም በቦንድ ግዥ፣ በግጭቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ፣ በህጋዊ መንገድ ገንዘብ በመላክ፣ እንዲሁም በየጊዜው በሚቀርቡ አገራዊ ጥሪዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ድጋፋቸውን ይበልጥ አጠናክረው አንደሚቀጠሉ የውይይቱ ተሳተፊ ዳያስፖራዎች ገልጻዋል::

በውይይቱ ላይ በጄኔቫ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛ ምክትል ሚሲዮን መሪ ክብርት አምባሳደር ማህሌት ኃይሉን ጨምሮ የሚሲዮኑ ዲፕሎማቶች እና ሚሲዮኑ በተወከለባቸው አገራት የሚኖሩ ዳያፖራዎች ተሳትፈዋል።

ምንጭ፡ Ethiopian permanent Mission Geneva