በሀገራዊ ምክክር የዳያስፖራ ሚና እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በራሳችን እሴቶች ላይ በመመስረትና መልካም ተሞክሮዎችን ከሌሎች ሀገራት በመቅሰም መጻኢ ዕድላችንን ብሩህ ለማድረግ ልንረባረብ እንደሚገባ ተገለጸ

በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በራሳችን እሴቶች ላይ በመመስረትና መልካም ተሞክሮዎችን ከሌሎች ሀገራት በመቅሰም መጻኢ ዕድላችንን ብሩህ ለማድረግ ልንረባረብ እንደሚገባ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ ክብርት አምባሳደር ብርትኳን አያኖ ገለጹ።

ይህ የተገለጸው ‘በሀገራዊ ምክክር የዳያስፖራ ሚና እና የሌሎች ሀገራት ተሞክሮ’ በሚል ርዕስ በተዘጋጀና የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት፣ የፌዴራል ተቋማት አመራሮች፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮች፣ ከኢድ እስከ ኢድ ጥሪን ተቀብለው የመጡ የዳያስፖራ አባላትና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት የምክክር መድረክ ላይ ነው።

የምክክር መድረኩን የከፈቱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታና ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ጣምራ ሰብሳቢ ክብርት አምባሳደር ብርትኳን አያኖ ባስተለለፉት መልክዕት ታላላቅ ሀገራዊ ጥሪዎች መከናወን በመጀመራቸውና ዳያስፖራውም በከፍተኛ ቁጥር ወደ ሀገር ቤት በመምጣቱ ዕውቀት፣ ክህሎትና ቴክኖሎጂን ለማሸጋገር እንዲሁም የኢንቨስትመንት ተሳትፎና ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት መፍጠር መቻሉን ጠቅሰው፣ ዳያስፖራው ከልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር መስተጋብር የሚፈጥርበት ዕድል በመመቻቸቱም ዳያስፖራው ሀገራዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችን እንዲረዳና የመፍትሔ አካል እንዲሆን ማድረግ ተችሏል ብለዋል። ኢትዮጵያውያን ችግሮቻቸውን በውይይት የሚፈቱባቸው ነባር ባህላዊ እሴቶችን ያዳበሩ ህዝቦች መሆናቸውንም አስታውሰው፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምንኖር ኢትዮጵያውያን በራሳችን እሴቶች ላይ በመመስረትና መልካም ተሞክሮዎችን ከሌሎች ሀገራት በመቅሰም መጻኢ ዕድላችንን ብሩህ ለማድረግ ልንረባረብ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ደያስፖራ አገልግሎት ም/ዋና ዳይሬክተርና ከኢድ እስከ ኢድ ብሔራዊ ኮሚቴ ሴክሬታሪያት አስተባባሪ ዶ/ር መሐመድ እንድሪስም በበኩላቸው መድረኩ ዳያስፖራውን ከሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት ጋር በማስተዋወቅ ለቀጣይ ግንኙነት በር ለመክፈት መዘገጀቱን ገልጸዋል። የጸና ሀገረ መንግስት መገንባት የቻሉ ሀገራት በረዥም ጊዜ የምክክር ሂደት ውስጥ ማለፋቸውን አስታውሰው፣ ኢትዮጵያን በያሉበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የተጀመረውን ሀገራዊ መግባባት ሂደት ሊደግፉት ይገባል ብለዋል። ዳያስፖራውም በሂደቱ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ጥሪ አቅርበዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች የሆኑት ወ/ሮ ሂሩት ገ/ስላሴና ዶ/ር ዮናስ አዳዬም በመድረኩ ላይ በመገኘት ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል። በዚህም መሰረት ኮሚሽኑ ከአምስት ወራት በፊት መመስረቱን፣ ግልጽነትና አሳታፊነትን በመርሆነት በመያዝ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ለመድረስ ዕቅድ መያዙን፣ በማህበረሰቡ አመኔታና ቅቡልነት ያተረፉ አካላትን በማሳተፍ እንደሚሰራ፣ ዳያስፖራውም በዚህ ሂደት ውስጥ የራሱን ሚና መወጣት እንደሚጠበቅበት፣ ከተሳኩና ካልተሳኩ የሌሎች ሀገራት የምክክር ሂደቶች ልምድ መቅሰሙን በአጠቃላይም በሰላማዊ አማራጭ ሰላምን የማፈላለግ ስራ እንዲያከናውን ኮሚሽኑ መቋቋሙን ገልጸዋል።

በኖርዲክ ሀገራት የኢትዮጵያ ምሁራን የውይይት ቡድን አስተባባሪ የሆኑት ዶ/ር ደሳለኝ ጫላ ሀገራዊ ምክክር ሀሳብ የሚዋጣበትና መፍትሔ የሚፈላለግበት መንገድ እንደሆነ ገልጸው፣ የተለያዩ ሀገራት የተከተሏቸው የምክክር ሂደቶች ያስገኟቸውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ውጤቶችን አስረድተዋል። በእንግሊዝ የተባበሩት ኢትዮጵያውያን የዕርቅና ሰላም ሰብሰቢ ዶ/ር ልዑልሰገድ አበበም በበኩላቸው ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ተነሳሽነት የጀመሩት ሀገራዊ የምክክር ሂደት አርአያነቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ ለሂደቱ ስኬታማነት ውጫዊም ሆኑ ጉዳዩ ይመለከተኛል የሚሉ አካላት ገንቢ ተሳትፎ በማድረግ ሊያግዙት ይገባል ብለዋል። በምክክር ሂደቱ ውጤት ላይ አተገባበሩ ያለውን ፋይዳም አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።

ከመድረክ በቀረቡት ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተጋባዥ ምሁራን ተጨማሪ ሀሳቦችን በማቅረብ ያዳበሯቸው ሲሆን፣ ተሳታፊዎችም ልዩ ልዩ ጥያቄና አስተያየቶችን አቅርበው ከመድረክ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።