ክቡር አምባሳደር ዘነበ በስዊዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖቻችን ለመደገፍ እያደረጉ ስላሉት አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቀረቡ።

(ጥር 30 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ)፡ በስዊዘርላንድ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት በአፋርና በአማራ ክልል የወደሙ የትምህርት ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችል የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ማዘጋጀት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የሚመክር የበይነ መረብ ውይይት አካሄደዋል::

በውይይቱ ላይ የተገኙት በስዊዘርላንድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ክቡር ዘነበ ከበደ በስዊዘርላንድ የሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት በአገራችን ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመርዳት ያሳዩት ተሳትፎ እጅግ የሚበረታታ መሆኑን በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል::

በክቡር ኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ በቀረበው ወደ አገር ቤት የመግባት ጥሪ መሰረት በርካታ የዳያስፖራ አባላት መሳተፋቸው ጠላቶቻችንን ያስደነገጠና ዕቅዳቸውን ያካሸፈ፣ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ደግሞ ተስፋና ሞራል የገነባ ምን ጊዜም የወገን ደራሽ ወገን መሆኑን ያረጋገጠና የሚያኮራ መሆኑን ክቡር አምባሳደር ዘነበ በንግግራቸው አንስተዋል::

የዳያስፖራ አባላቱ በችግር ላይ የሚገኙ ወገኖቻችን ለመደገፍ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሳያስቀምጡ እያደረጉት ላለው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ሚሲዮኑ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ በማረጋገጥ የወደሙ ት/ቤቶችን ለመገንባት በቀጣይ በስዊዘርላንድ በሚካሄደው የገቢ ማሰባሰቢያ የእራት ፕሮግራም ላይ ሁሉም ዳያስፖራ በመሳተፍ ድጋፍ እንዲያደርግ ክቡር አምባሳደር ዘነበ ጥሪያቸውን አቅርበዋል::

በዚህ ውይይት ላይ የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አሊ አህመድ እና በአማራ ክልል ትሞህርት ቢሮ የእቅድና ሀብት ማሰባሰባ ዳይሬክተር አቶ ምስጋናው አማረ የተሳተፉ ሲሆን፤ በሁለቱ ክልሎች በህወሃት ወረራ የደረሱ ጉዳቶችን በተመለከተ ገለጻ በማድረግ የዳያሳፖራ አባላቱ የትምህርት ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው እንቅሰቃሴ እያደረጉት ስላለው ደጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል ::