በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞችና ባለሙያዎች ጋር ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ፡፡

በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞችና ባለሙያዎች ጋር ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሄደ፡፡

(ታህሳስ 29፤ 2014 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ): በስዊዘርላንድ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀኪሞችእና በተለያዩ ዓለም ዓቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ከሚሰሩ ባለሙያዎችና የኢትዮጵያ ወዳጆች ጋር በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት በደረሰባቸው የጤና ተቋማት መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት ተካሂዷል።

በጄኔቫ የኢ.ፌዲ.ሪ ቋሚ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዘነበ ከበደ ውይይቱን የመሩ ሲሆን የህወኃት ኃይሎች በአማራና በአፋር ክልሎች በፈጸሙት ወረራ ወቅት በሰላማዊው ሕዝብ ላይ ከፈጸሙት አሰቃቂ ጭፍጨፋ ባሻገር በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማትና መገልገያዎች ላይ ያካሄዱት መጠነ ሰፊ ዘረፋና ውድመት ለዓይን የሚቀፍና ለአዕምሮ የሚሰቀጥጥ መሆኑን ከገለፁ በኋላ ወራሪውን ሽብርተኛ ቡድን በተባበረ ክንድ ከሁለቱም ክልሎች ጠራርገን እንዳስወጣነው ሁሉ የተዘረፉ፣ የወደሙና ከአገልግሎት ውጭ የተደረጉትን ተቋማት መልሶ ለማሟላትና የተፈናቀሉ ዜጎቻችንን መልሰን ለማቋቋም በአገር ውስጥና በውጭ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ታላቅ ሀገራዊ ጥሪ መቅረቡን ገልጸዋል።

በተለይ ደግሞ የፈራረሡ የጤና ተቋማትን መልሶ መገንባት፣ የተዘረፉና የወደሙ የሕክምና መገልገያ ዕቃዎችንና መድሃኒቶችን መልሶ ማደራጀትና ማሟላት ከሕዝብ ጤና ጋር የሚያያዙና ጊዜ የማይሰጡ በመሆናቸው የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ያቀረበውን አፋጣኝ ጥሪና የላከውን የፍላጎት ዝርዝር መነሻ በማድረግና ወደ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ለመግባት የስብሰባው ተሳታፊዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት የጋራ ውይይት ለማድረግ በመገኘታችሁ ልባዊ ምስጋናዬን አቅርባለሁ ብለዋል።

በተጨማሪም የድጋፍ አሰባሰቡን ዓላማ፣ ጉዳት ስለደረሰባቸው ተቋማትና ጠቅለል ያለ የሀብት ግምታቸውን፣ ስለሚፈለጉ ድጋፎችና ሥራውን ለማከናወን ሊኖር ስለሚገባው አካሄድ፣ ቅንጅትና ዝግጅት በተመለከተ በቋሚ መልዕክተኛ ጽ/ቤቱ የጤና አታሼ ወ/ሮ ብሩክ አባተ የመነሻ ገለጻ ከተደረገ በኋላ ሰፋ ያለ ውይይት አካሂደዋል። በመጨረሻም ስራዉን በተፋጠነ ሁኔታ ለማከናወን እንዲያስችል ሊኖር በሚገባው አካሄድ፣ የሥራ ክፍፍልና ቅንጅታዊ አሠራር እንዲሁም የግንኙነትና የውይይት ሥርዓት ላይ የጋራ አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይታቸውን አጠናቀዋል።