ሐዊር – ሚሚ ፈቃደ ከጄኔቫ

የመጽሐፉ መጠሪያ “ሐዊር” ማለት በግዕዝ ጉዞ ማለት ነው። የግዕዝ መዝገበ ቃላት ሐዊርን መሄድ፤ መራመድ፤ ከቦታ ቦታ መዘዋወር፤ መውደቅ መነሳት፤ በደረት መሳብ የሚል ትርጓሜ ይሰጠዋል። የኔም የ23 ዓመት የህይወት ጉዞ የሐዊርን ትርጓሜ ሙሉ በሙሉ የሚያካትት ነው።

የመጽሐፉ ይዘት ግለ ታሪክ ቢሆንም በልብ ወለድ አፃፃፍ ዘዬ የተቃኘ፤ ወደፊት በሚሄድ የህይወት ጉዞ ውስጥ አልፎ አልፎ ምልሰት ያለው ፅሁፍ ነው። በ 23 ዓመት የስዊዘርላንድ የህይወት ጉዞዬ ያጋጠሙኝን ፈተናዎች እና መልካም ነገሮች ከብዙዎቹ ይጠቅማሉ ያልኳቸው ጥቂቶቹን በ340 ገፅ ከሽኜ ለአንባቢ አቅርቢያለሁ። መጽሐፉ በውስጡ ሃያ ምዕራፎችን ያካተተ ሲሆን ስደት እና ስኬት፤ ፍቅር እና ፀብ፤ ደስታ እና ሃዘን፤ ለቅሶ እና ሳቅ፤ እናትነት እና ልጅነት መወለድን እና መሞትን ወ.ዘ.ተ ሁሉንም የህይወት ገጠመኞች በየዘርፉ ያካተተ ነው። አልፎም በመልከዐ-ምድር ተራራማነት እና በፖለቲካ ስርዓት አንድ አይነት የፌደራል አገዛዝ ያላቸው የትውልድ አገሬን ኢትዮጵያን እና የቃልኪዳን አገሬን ስዊዘርላንድን ለማወደደር ይረዳ ዘንድ አንኳር ጉዳዮችንም ያስቃኛል።

ሐዊር ለአንባቢዎች በኢትዮጵያ፤ በአውሮፓ፤ በአረብ ሐገራት እና በአሜሪካ ለሽያጭ ቀርቧል።