የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ19) ሉላዊ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም ከስዊዘርላንድና ኦስትሪያ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተገኝቷል

በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ሚሲዮኖችና ዳያስፖራ ማህበረሰብ ከ18 ሚሊየን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን የውጭ አገሮች ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስታወቀ።

ዓለምን ለሁለንተናዊ ቀውስ እየዳረገ ባለው የኮሮናቫይረስ (ኮቪድ19) ሉላዊ ወረርሽኝ የሚያስከትለውን ጫና ለመቋቋም አገሮች የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።
ኢትዮጵያም በውጭና በአገር ውስጥ ያሉ ዜጎችን የተባበረ ክንድ በመሻት ብሔራዊ የኮረናቫይረስ መከላከል የሀብት አሰባሳቢ ግብረኃይል በማቋቋም ወደስራ ከገባች ሰነባብታለች።

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንም የተቻላቸውን እጃቸውን በመዘረጋት ላይ ሲሆኑ በውጭ የሚገኘውን ድጋፍ የሚያሰባስበው የግብረሃይሉ አንዱ ክንፍ ነው።

የውጭ አገራት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት የውጭ ጉዳይ ሚኒስር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ማምሻውን ለኢዜአ በሰጡት መግለጫ፤ ኮሚቴው በየክፍላተ ዓለም ከሚገኙ ሚሲዮኖችና የዳያስፖራ ማህበረሰብ በፍላጎት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ የማሰባሰብ ተግባር ላለፉት 15 ቀናት አከናውኗል።

በዚህም ኮሚቴው በሚሲዮኖች የአደራ ሂሳብ ቁጥር፣ በባንኮች ሬሚታንስ፣ በኢትዮ ቴሌኮም ድጋፍ ማሰባሰቢያ ፕላትፎርም የተዘጋጁ ሲሆን በዚህም በየአገሮች የሚገኙ 60 ሚሲዮኖች ሰራተኞችና የዳያስፖራ አባላት በገንዘብ፣ በአይነትና በሙያ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የዳያስፖራ ማህበረሰቡ ከዚህ በፊት በተለያየ አገራዊ የልማት ስራዎችና የአደጋ ጊዜ አለኝታ ሆኖ መቆየቱን የገለጹት አምባሳደር ብርቱካን፤ ”የወቅቱን ድጋፍ ለየት የሚያደርገው ወረርሽኙ ዓለም አቀፋዊ ቢሆንም ዳያስፖራው ከራሱ አልፎ ወገኑን የማስቀደም ተግባር ላይ መሰማራቱ ነው” ብለዋል።

በዚህም እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰራተኞችን ጨምሮ ከ60 ሚሲዮን ሃላፊዎችና ሰራተኞች ከ3 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰብ ተችሏል።

በተለያዩ አገሮች ከሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት በድምሩ 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር በላይ ተሰብስቧል።

ከነዚህም መካከል ከአቡዳቢ 2 ሚሊዮን፣ ከዱባይ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን፣ ከቤጂንግ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን፣ ከካናዳ ኦታዋ 1 ሚሊዮን እንዲሁም ከስዊዘርላንድና ኦስትሪያ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተገኝቷል።

አዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ሚያዝያ 2/2012 ዓ.ም

ከስዊዘርላንድና ኦስትሪያ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተገኝቷል